Educational Jobs View All


የተፈሪ መኮንን የሥልጣን ጉዞ


...

ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ የምሩ የመንዝና የተጉለት ተወላጅ ናቸው። በውበታቸውና በሙያቸው የሚደነቁት ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ ከንጉስ ሣህለ ሥላሴ ልጅ ከራስ ዳርጌ ጋር የሕግ ጋብቻ ባይኖራቸውም፣ እንደ ሚስት አብረው በመኖር አንድ ወንድ ልጅ ወልደውላቸዋል። እኚህ ከራስ ዳርጌ የተወለዱት ኋላ ስመ ጥር ጀግና ሆነው አባ ቀትር የተባሉት ደጃዝማች ደስታ ዳርጌ ናቸው።

ምኒልክ ኃይለ መለኮትና ዳርጌ ሣህለ ሥላሴ በአጼ ቴዎድሮስ ተይዘው መቅደላ በሚኖሩበት ዘመን፣ ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ እስረኞቹን ለመጠየቅና በዚያው አካባቢ ማረፊያ ቦታ አግኝተው ስንቅ ለማቀበል አስበው፣ በ1853 ዓ.ም. ከሸዋ ተነስተው ወደ ጎንደር ረዥም ጉዞ ጀምረው ነበር። ወለተ ጊዮርጊስ እንደ ሚስት ሆነው አብረዋቸው የኖሩትን ራስ ዳርጌንና ከእሳቸው የወለዷቸውን ልጃቸውን ደጃዝማች ደስታን ለማየት ጓጉተው ወደ መቅደላ በሚጓዙበት ጊዜ በመንገዳቸው ላይ ከወሎ ግዛት ሲደርሱ ያልጠበቁትና ያላሰቡት ነገር አጋጠማቸው።

ሼህ ዓሊ የተባሉ የወረይሉ ባላባት በወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ ውበት ተማርከው በግዴታ ጠልፈው "ሚስቴ" ሆነሻል በማለት ከጀመሩት ጉዞ አቋረጧቸው። በዚያን ሰዓት ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ የሼህ ዓሊን ፍላጎት ከመፈጸም በስተቀር ሌላ የመከላከያ አቅም አልነበራቸውም። ወለተ ጊዮርጊስ በተጠለፉ በአስረኛው ወር ከሼህ ዓሊ የጸነሷት ሴት ልጅ ስትወለድ የሺእመቤት ተብላ ተሠየመች።

ወይዘሮ ወለተ ጊዮርጊስ ከወረይሉ ባላባት ከሼህ ዓሊ የወለዷትን ሴት ልጅ ይዘው ወደ ሸዋ ለመመለስ የቻሉት አጼ ምኒልክ ከቴዎድሮስ አምልጠው ከተመለሱ ከአንድ አመት በኋላ ነው። በዚያን ጊዜ ሕጿኗ የሺእመቤት የአራት አመት ልጅ ነበረች። የሺመቤት በራስ ዳርጌ ቤት እያደገች እድሜዋ ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ በተወለደች በአስራ ሁለት አመቷ ዳርጌ ሣህለ ሥላሴ የእህታቸው የተናኘወርቅ ልጅ ልጅ ለሆኑት ለመኮነን ወልደ ሚካኤል [ ኋላ ራስ] ዳሯት። መኮነን ወልደ ሚካኤልን ከባላምባራስነት ደረጃ አንስተው በየጊዜው በሹመት እያሳደጉ በመጨረሻም የራስ ወርቅ አስረው የሐረር ጠቅላይ ገዥ ለመሆን ያበቋቸው ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ምኒልክ ናቸው።

ወይዘሮ የሺመቤት ከባለቤታቸው ከራስ መኮነን ጋር የነበራቸው ትዳርና ሕይወት ምቾትና ሰላም ያለው በመሆኑ ሲደሰቱ፣ በየዓመቱ የሚጸንሱት ልጅ ስለሚሞትባቸው ሐዘንና ሰቀቀን ሳይለያቸው ኖረ። በ1884 ዓ.ም. ለዘጠነኛ ጊዜ መጸነሳቸው ሲታወቅ የሼሆቹም ሆነ የየገዳሙ ትንቢት ተናጋሪዎች «ይህ የተጸነሰ ሕጻን በደህና ወደዚህ አለም ለመምጣት ከጌታ ተፈቅዶለታል። እንደተወለደ ከእናቱ ተነጥሎ ለብቻው በልዩ ጥንቃቄ እንዲያድግ ያስፈልጋል። ከብዙ ሰው ዓይን ተሰውሮ ካድገ በኋላ ብዙ ፈተናቸዎን አልፎ አንድ ቀን ባልተጠበቀ ጊዜ የቅድመ አያቶቹን ዘውድ ለመውረስ ይበቃል...» ብለስ ነበር ይባላል።

ይህ ትንቢት ከልዩ ልዩ ቦታዎች እየተሰራጨ ስለሚነገር የሚባለውን ለመፈጸም ራስ መኮነን እንዲስማሙ ብርቱ ጥረት ተደረገ። በዚያን ጊዜ የራስ መኮነን አስተያየት «ልጅ የሚሰጥ ፈጣሪያችን ነው። የሚነሣንም እሱ ነው፤ አሁን እኛ በፈጣሪ ስራ ገብተን እናትና ልጅ የምናለያየው ለምንድን ነው?» የሚል ነበር። በመጨረሻም የሼሆቹና የባህታዊዎቹ ተከታዮች አሸነፉ።

ከዛሬ 124 ዓመታት በፊት ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም. ሌሊት ወይዘሮ የሺመቤት ተፈሪ የተባለውን ወንድ ልጅ በደህና ሲገላገሉ፣ ወዲያውኑ እናቱ ሳይስሙት [ወይንም ሳይስሙት] በሱፍ ጨርቅ ተጠቅልሎ በአገልግል ውስጥ ተደርጎ ለማደጊያ ወደተዘጋጀለት ሥውር ቦታ ተወሰደ። የጻድቁ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ልዩ አማኝ የሆኑት ወይዘሮ የሺመቤት ለመጀመሪያ ጊዜ በደህና የተገላገሉትን ሕጻን ልጃቸውን ካላሳያችሁኝ ብለው አላስቸገሩም። «ልጅ በደህና ወልጄ ታቅፌ ለማሳደግ ስፈልግ ብዙ ተሳቅቄያለሁ።ይኽ ዘጠነኛ ጽንሴ እግጅም አላስቸገረኝም ነበር። ሕይወት እንዲኖረው ከእናቱ መነጠል አለበት ካላችሁ በጤና አድጎ በሰላም እንዳየው እናንተም ጸልዩልኝ...» ብለው ዝም አሉ።

ተፈረ ከተወለደ ሁለት አመት ሊሞላው ሲቃረብ ወይዘሮ የሺእመቤት እንደገና ጸነሱ። እንደሚባለው ይህ አስረኛው እርግዝና እመይቴን ሰላም አልነሳቸውም ነበር። ከሌሎቹ ጊዜያት ይበልጥ ጤንነት ስለተሰማቸው ጾምና ጸሎቱን እጅግ አጥብቀው ሲጠባበቁ በመጋቢት 6 ቀን 1886 ዓ.ም. የተጸነሰው ለመወለድ መጣሁ አለ። የእርግዝናቸውን ወራት በጤና ያሳለፉት ወይዘሮ የሺእመቤት በመውለጃቸው ሰዓት ምጡ እጅግ አሰቃያቸው። በዚያን ጊዜ በኤጄርሳ ጎሮ ወይዘሮ የሺእመቤት አጠገብ ተኝተው የዓይን ምስክር የሆኑት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም በታሪክ ማስታወሻቸው ላይ እንዳሰፈሩት አዋላጆች ተሰባስበው ማርያም ማርያም እያሉ ለማገላገል የተጠቀሙበት ዘዴ የወይዘሮ የሺእመቤትን ሥቃይ ምን ያህል እንዳበዛው ለማስረዳት «እጅግ የሚዘገንን» መሆኑን ገልጸውታል። አዋላጇ እንደምንም ልጁን መንጥቃ ብታወጣውም ሕጻኑ በነፍስ አልቆየም። በቶሎ በድን ሆነ፤ ወይዘሮ የሺእመቤትም ስቃያቸው ወደ ጣር ተለወጠ። ሰውነታቸው እየደከመ ትንፋሻቸው እያጠረ ሄደ። በዚሁ በመጋቢት 6 ቀን 1886 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ላይ ወይዘሮ የሺእመቤት የጣር ትንፋሽ ቆሞ ህይወታቸው አለፈ።

በተወለዱ በሠላሳ ሁለተኛው ዕድሜያቸው፣ ከራስ መኮነን ጋር ጋብቻቸውን በፈጽሙ በአስራ ስምንተኛው ዓመት በሕይወት የተረፈላቸውን ልጃቸውን ተፈሪን በወለዱ በአንድ አመት ከሰባት ወር፤ በየጊዜው ሲሰቃዩና ሲሳቀቁ በኖሩት በወሊድ ምክንያት ይህንን ዓለም ተለይተው ሄዱ። በሐረርጌዎቹ ዘንድ የተወደዱት እመቤት ሞታቸው በተገለጸ ጊዜ ምን ያህል እንደታዘለናቸው ብዙዎች የአይን ምስክሮች ተናግረውታል። በተለይ ከብዙዎች መካከል አንድ ለናቱ ሆኖ የተረፈላቸውን ልጃቸውን ተፈሪን አይኑን ሳያዩትና ሳያቅፉት፤ ተፈሪም የናቱን አይን ሳያይ መሞታቸው ባለቤታቸው ራስ መኮነንን ዕድሜ ልካቸውን ሙሉ ሲያስጸጽታቸው የኖረ ነው።

ህጻኑ ተፈሪ እናቱን ለማወቅና የእናት ወግ አግኝቶ ለማደግ የታደለ አልሆነም። እንደዚሁም የእናት ልጅ የሆነ ወይንም የሆነች ወንድም ወይንም እህት ኖሮት አብሮ አላደገም። በኤጀርሳ ጎሮ ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም. ተወልዶ እናቱን ሳያውቅ በኮምቦልቻ በቀኛዝማች አባ ናደው እጅ ያደገው ተፈሪ ከተወለደ እነሆ ዛሬ 124 ዓመት ሆነው። ይህ ተፈሪ የሐረር ሼሆችና የየገዳሙ ትንቢት ተናጋሪዎች «ከብዙ ሰው ዓይን ተሰውሮ ካድገ በኋላ ብዙ ፈተናቸዎን አልፎ አንድ ቀን ባልተጠበቀ ጊዜ የቅድመ አያቶቹን ዘውድ ለመውረስ ይበቃል...» ብለው የተነበዩለትና ዛሬ ዝናቸው በአለም ላይ የገነነው ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ናቸው። መልካም ልደት ግርማዊ ጃንሆይ!

[ምንጭ፡ዘውዴ ረታ «ተፈሪ መኮንን ተፈሪ መኮንን ረጅሙ የሥልጣን ጉዞ» ከገጽ 17 - 20]

አቻምየለህ ታምሩ

 


Article read: 2748

On 07-24-2016

By Kidus Michael


Related articles


advertismentFOLLOW US ON THE NET


POPULAR VIDEOS View All

 • Seifu on EBS: Musician Tadele Roba, His Wife and Seifu Friends Live Dance
  New
  • Share
  • |
  • 3338

  Seifu on EBS: Musician Tadele ...

 • Mogachoch EBS Latest Series Drama - S06E137 - Part 137
  New
  • Share
  • |
  • 2601

  Mogachoch EBS Latest Series Dr...

 • Jossy In The House: Interview With Mr. Lidetu Ayalew Part 2
  New
  • Share
  • |
  • 2589

  Jossy In The House: Interview ...

 • Mogachoch EBS Latest Series Drama - S06E139 - Part 139
  New
  • Share
  • |
  • 2471

  Mogachoch EBS Latest Series Dr...

 • Zemen Drama - Part 70
  New
  • Share
  • |
  • 2316

  Zemen Drama - Part 70...

 • Ethiopikalink Sheik Al Amudi Could be freed if he gave away 70% of his wealth Saudi off
  New
  • Share
  • |
  • 2191

  Ethiopikalink Sheik Al Amudi C...

 • Click Here for Top Videos